Tuesday, April 04, 2017

የአለም ፖለቲካ-ኢኮኖሚና የኢትዮጵያ ህዳሴ በአቶ ዓለምነው መኮንን ብዕር ሲቃኝ

ሲሳይ መንግስቴ አዲሱ

Tigrai Online April 4, 2017

መግቢያ

ካለኝ ቅርበት አኳያ አቶ ዓለምነውን አንተ እያልሁ ብገልጸው ደስ ባለኝ ነበር፣ ሆኖም በሀገራችን ባህል መሰረት ትልቅ የፖለቲካ ስልጣን ላይ የሚገኝን ሰው አንተ ማለት አንድም እንደ መዘርጠጥ አሊያም አክብሮት እንደ መንፈግ ተደርጎ ስለሚወሰድ በዚህ መጣጥፍ ውስጥ አቶ ዓለምነውን አንቱ እያልሁ ለመግለጽ ተገድጃለሁ፡፡ ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብአዴን/ኢህአዴግ አባላትና በአማራ ክልል ህዝቦች ዘንድ አቶ ዓለምነው መኮንን እየታወቁ የመጡት በአወዛጋቢ ንግግራቸው ብቻ ሳይሆን በአንባቢነታቸውና አዳዲስ ሀሳቦችን በማመንጨት የተግባር መመሪያ ለማድረግ በመንቀሳቀሳቸውም ጭምር ነው፡፡


በተለይም በአንድ ወቅት በግሉ ፕሬስና በማህበራዊ ሚዲያው አካባቢ “የአማራን ህዝብ ሰድበው ለሰዳቢ ሰጡት” በሚል ሽፋን የእሳቸውን ስብዕና ለመግደል ጥረት ከመደረጉም በላይ በአሁኑ ወቅት እሳቸውና የስራ ባለደርቦቻቸው በፊታውራሪነት የሚመሩትን የፖለቲካ ድርጅት ከህዝብ ለመነጠል አጋጣሚውን መጠቀማቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በዋነኛነት ለብአዴን አባላት በሚሰራጨው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መጽሔት ላይ በሚያቀርቧቸው መጣጥፎች ቀደም ሲል ባልተለመደ ሁኔታ ጥልቅ ትንታኔ በመስጠትና ይህንኑም ትንታኔያቸውን በበርካታ ማጣቀሸዎች በማስደገፍ አሳማኝ ንድፈ ሀሳባዊ አቀራረብን ከአለማችንና ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም በመሞከራቸውም ይታወቃሉ፡፡

አሁን ደግሞ ፖለቲካ-ኢኮኖሚና የኢትዮጵያ ህዳሴ በሚል አብይ ርዕስ በዋነኛነት 405 ገጾችን የያዘ ዳጎስ ያለ መጽሀፍ በማሰጋጀት አሳትመው ቀደም ባለው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ውስጥ ማስመረቃቸውን በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት በሰማን ማግስት አዲስ አበባ ለምንገኝ ወገኖቻቸው ዕድሉ እንዲደርሰን ለማድረግ በማሰብ ይመስላል በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ በድጋሜ ለማስመረቅ ዝግት ማድረጋቸውን በመስማታችን የዝግጅቱ ታዳሚ እንደምንሆን አስቀድመን አረጋገጥን፡፡ ስለሆነም የዚህ መጣጥፍ ዋና አላማም በመጽሀፉ ምረቃ ወቅት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስለ እንደነበረ በአጭሩ መግለጽ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ንባብን መሰረት በማድረግ በመጽሀፉ አቀራረብና ይዘት ላይም ያለኝን የተመጠነ ምልከታ በወፍ በረር ቅኝት ለተደራሲያን ማሳየት ይሆናል፡፡ መልካም ንባብ!!

የመጽሀፉ ምረቃ ስነ-ስርአት ድባብ በብሔራዊ ትያትር  
መጋቢት 9/2009 ዓ.ም የአቶ ዓለምነው መኮንን መጽሀፍ በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ እንደሚመረቅ አስቀድሞ ስለተነገረኝ እኔም በቅርብ የማውቃቸውን ሰዎች እንዲገኙ ጋብዤ በስአቱ በቦታው ተገኘን፣ በመሆኑም ድባቡ እጅግ ደስ የሚል ሁኔታን ያንጸባርቅ እንደ ነበር ቀዳሚ ምስክር ነኝ፣ በእውነትም የመጽሀፍ ምረቃ መሆኑን ገና የቲያትር ቤቱ አዳራሽ በር ሲገባ ግራና ቀኝ በሁለት ጠረንጴዛዎች ላይ መጽሀፉ ተደርድሮ ታዳሚው እየተሻማ ሲገዛው መታየቱ የድጋሜ ምረቃውን ተፈላጊነት በእጅግጉ ያሳብቅ ነበር፡፡ ነገር ግን አቶ ዓለምነው ብአዴን/ኢህአዴግ በሚመራው መንግስት ውስጥ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ሆነው ሳለ ባለ አምስት ኮከብ የሆኑትን ሸራተን አዲስን ወይም ካፒታል ሆቴልን አሊያም ራዲሰን ብሉን ወይም ኢሊሌ ሆቴልን ለምን አልመረጡም? እያልሁ ጥያቄዎችን ለማንሳት ብገደድም ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን ለእኔ ይኸኛው ውሳኔያቸው በእጅጉ ተመችቶኝ እንደነበር ከመግለጽ ግን አልቆጠብም፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል ብሔራዊ ትያትር የጥበብና የጥበበኞች ቤት በመሆኑ የጥበብ ስራ ውጤትን በዚህ ቤት ማስመረቅ በራሱ ደስ የሚል ስሜት ነበረው፡፡ በሌላ በኩል ሁሉንም ዜጋ በእኩል አይን አየተመለከተ ተቀብሎ ያለ ልዩ መጥሪያ ካረድና አድሎዋዊ መስተንግዶን ከሚያስከትለው ፕሮቶኮል ነጻ አድርጎ ለመታደም የመጣው ሰው በእኩልነት እንዲስተናገድ ዕድልን የሚሰጥ መሆኑ ሌላኛው መልካም ገጽታው ነው፡፡

ስለሆነም እጅጉን ተስማምቶኝ ስለነበር ተደስቸበታለሁ፣ በምረቃው ስነ ስርአት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩትን ጨምሮ በርካታ የፌዴራል የመንግስት ባለስልጣናት የተገኙ ቢሆንም ነባሮቹ የብአዴን/ኢኢአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ግን እንዳልተገኙ ታዝቤያለሁ፣ ለምን ለሚለው ጥያቄ ለጊዜው መልስ ባለማግኘቴ በሒደት እውነታውን ከደረስሁበት አንድ ሁለት ልልበት እችል ይሆናል፣ ለዛሬው ግን ከዚህ በላይ የምለው የለኝም፡፡ ይህም ሆኖ አዳራሹን ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላው ወጣትና የእኔ አይነት ተራው ሰው መሆኑ በእውነት ነው የምላችሁ በእጅጉ አስደስቶኛል፡፡

ምክንያቱም ርዕሰ ጉዳዩ ወቅታዊ ከመሆኑም በላይ አሁን ላይ ባለው የሀገራችን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ የአለምን ፖለቲካ በሰፊውና በጥልቀት ለመቃኘት የተቻለበት መጽሀፍ ስለሆነ በወጣቱ ትውልድ በአጠቃላይና በድርጅቱ ደጋፊ ወጣት ምሁራን ላይ በተለይ ሁለንተናዊ ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ የሚኖረው ፋይዳ እጅግ የላቀ ስለሆነ፡፡ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ያለ ዳጎስ ያለ መጽሀፍ አዘጋጅቶ ለማሳተም ቀርቶ ለማንበብ ጊዜ የለንም የሚሉ ፖለቲከኞችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በብዛት በሚገኙባት አገር ከመደበኛ ስራ ጎን ለጎን በርካታ መጽሀፍትን አንብቦ በንጽጽር ለመተንተን ፍላጎት ማሳየት ብቻ ሳይሆን የእረፍት ጊዜ መስዋዕት ማድረግን፣ የአእምሮ ዝግጁነትንና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ሀላፊነት ውስጥ ገብቶ መገኘት በራሱ ትልቅ ነገር መሆኑ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡

የጥረት ዉጤትንም እንዲህ በተግባር ማሳየት መቻል በራሱ ብዙም ስራ ሳይኖራቸው ስራ ይበዛብናል ለሚሉና ምንም ሳያነቡ አዋቂ ለመምሰል ለሚሞክሩ የዘመኑ ባለስልጣናትና ፖለቲካኞቻችን ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ብቻ ብየ ማለፍ እፈልጋለሁ፣ አቶ ዓለምነው ውድ የሆነውን ጊዜያቸውንና በጥረታቸው የተጎናጸፉትን ሁለገብ የሆነውን ክህሎታቸውን እንዲሁም በትምህርትና በጥልቅ ንባብ ያሳደጉትን እውቀታቸውን በመስጠት ብቻ ሳይወሰኑ የማንንም ባለሀብት ይሁን የልማት ድርጅት ድጋፍ ሳይጠብቁ ይልቁንም ያላቸውን ጥሪት አሟጠው በመጠቀም መጽሀፉን ማሳተማቸውና ለስርጭትም ማዘጋጀታቸው በእርግጥም አርአያነት ያለው ተግባር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

የአቶ ደመቀ መኮንንን አባባል ልዋስና “አንድያ ቤታቸውን በባንክ አስየዘው ባገኙት የብድር ገንዘብ መጽሀፉን አሳትመው ለተደራሲያን አቅርበዋልና”፡፡ ይህም ድርጊታቸው በስፖንሰር ማፈላለግ ሽፋን በመቶ ሽዎች ወይም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዝብ ከሚሰበስቡ የዘመኑ ባለስልጣናትና ግለሰቦች የተለየ እርምጃ መውሰዳቸው በእርግጥም የሚያበረታታ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ መጽሀፉን ለማስመረቅ ከውድ ባለቤታቸው ሰብለወርቅ አባተ ጋር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የአውሮፕላን ቲኬታቸውን በራሳቸው ገንዘብ ቆርጠው አዲስ አበባ ላይ የሚቀበላቸው የጓደኛ ተሸከርካሪ ብቻ መጠቀም መቻላቸው ሲታከልበት እውነትም አቶ ዓለምነው ከማንም ምንም ነገር ላለመነካካት ያደረጉት ጥረት አካል ነውና መጽሀፉን ለማስመረቅ ለምን የብሔራዊ ትያትር አዳራሽን መረጡ ለሚለው ጥያቄየ ምላሽ ማግኘት ችያለሁ፡፡ የእሳቸው የስልጣን ደረጃ የሚገኝ ሰው ቀርቶ ከዛ በታች ባለ የስልጣነ ደረጃ ለላይ የሚገኝ ፖለቲከኛ ስልጣኑን በመጠቀም የግል ጥቅሙን ሲያሳድድ በሚገኝበት ወቅት ለመንግስትና ለድርጀት ስራ በእጅጉ ጠቃሚ የሆነ መጽሀፍን ለማሳተምም ሆነ ለማሰራጨት የግል ሀብትን መጠቀም ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡

በአርግጥ አቶ ዓለምነው ቀደም ሲል ጀምሮ ሳውቃቸው ንጹህ ታጋይ፣ ቀና አስተሳሰብ ያላቸውና የተሟላ ስብእናን የተላበሱ ሰው መሆናቸውን ጠንቅቄ ባውቅም አሁን በፈሙት ፍጹም ከሙስና የጸዳ ተግባር ይበልጥ እንዳከብራቸውና እንድኮራባቸውም አድርጎኛል፡፡ ስለሆነም የዚህ አይነቱን ቅን፣ ለሀገሩ ተቆርቋሪና ያለውን ሁሉ አሟጦ ለመስጠት የሚተጋን ሰው በፖለቲካ አቋም መለያየት ቢኖርና የተለያየ አስተሳሰብ ብንይዝም እንኳ ማበረታታት የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡

ይህንን ሀሳባችንን ተግባራዊ የምናደርገው ደግሞ መጽሀፉን ገዝተን በማንበብና ሀሳባቸውን በመጋራት ስለሆነ ሁላችንም ይህንን መልካም ተግባር ሳንውል ሳናድር ብንፈጽም አንድም የአቶ ዓለምነው ድካም ውጤታማ መሆኑን እናረጋግጣለን፣ ሁለትም ስለ ሀገራችን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ስለ አለም ወቅታዊ ሁኔታ በቂ የሆነ እውቀት በመሸመት አጠቃላይ ግንዛቤያችንን እናሳድጋለን፣ በመሆኑም መጽሀፉን አሁኑኑ አግኝተን ልናነበው ይገባል እላለሁ፡፡

በመጽሀፉ ላይ ያለኝ አጠቃላይ ምልከታ
መጽሀፉ በመጀመሪያው ምዕራፍ ንድፈ ሀሳባዊ ትንታኔን መሰረት ያደረገ ገለጻን በሰፊው ያቀረበ ሲሆን ለቀጣዮቹ ምዕራፎች መንደርደሪያ የሚሆን ግብአትን አካቶ ይዟል፣ በመቀጠልም ንድፈ ሀሳባዊ ትንታኔን ከተግባራዊ እንቅስቃሴ ጋር አዛምዶ ለማቅረብ የሞከረ፣ ለበርካታ ጥያቄዎች በቂ ሊባል የሚችል መልስ እየሰጠ የመጣ በተለይም በፖለቲካው አለም ውስጥ እስከ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ደርሰው ስለኒዮ ሊበራሊዝም ጽንሰ ሀሳበም ሆነ ስለ ሶሻል ዴሞክራሲ ልዩ ባህሪያት ከዛም አልፎ የእለት ከእለት ተግባራቸው መሰረት ስለሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ምንነት፣ በአጠቃላይም ስለሶስቱ የዴሞክራሲ አይነቶች አንድነትና ልዩነት እዚህ ግባ የሚባል እውቀት ሳይኖራቸው ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ተቀምጠው ግፋ በለው ለሚሉት ብቻ ሳይሆን የተወሰነ ግንዛቤ ይዘው ብዙ እንደሚያውቁ ለሚያስቡ የፖለቲካ አመራሮችና የመንገስት ባለስልጣናት የተግባር መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡

ይህም ሆኖ ይህን ጭምቅ ሀሳብ ከማጣቀሻዎቹ ጋር እያገናዘቡና ከተቻለም አለፍ እያሉ የሌሎች ምሁራን ስራዎችንም መዳሰስን በጠየቀ ንባብ መደገፍ እንዳለበት ይታመናል፣ ለዚህም ዋነኛዎቹ የመጽሀፉ ተደራሲያን የሆኑት የኢህአዴግ ፖለቲከኞችና ባለስልጣኖቻቸው ራሳቸውን በቅጡ ማዘጋጀት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል፣ ከሁሉም በላይ ግን ራስን ከወቅቱ አለማዊና ሀገራዊ ሁኔታ በተለይም ነባራዊ ሀቅ ጋር እያጣጣሙ የአመራርና የመፈጸም አቅምን በቀጣይነት ማሳደግን ስራየ ብለው ሊይዙት እንደሚገባ ከአቶ ዓለምነው መጽሀፍ ትምህርት ሊቀስሙ ይገባል፡፡ አጠቃላይ ሁኔታውን በዚህ መልኩ አስቀምጨ ሳበቃ በመጽሀፉ አቀራረብ፣ የቋንቋ አጠቃቀምና ይዘት ላይ የተስዋሉትን ሁኔታዎች በአዎንታም ሆነ በአሉታ የተወሰኑ ነገሮችን በማንሳት የሚታዩትን ክፍተቶች ጭምር ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ፡፡

የመጽሀፉን አደረጃጀትና አቀራረብ በተመለከተ
እኔ እስከማውቀው ድረስ ክፍል የሚለው ርዕስ ምዕራፍ ከሚለው ርዕስ ሰፋ ያለ ሆኖ ሳለ በዚህ መmጽሀፍ ውጥ ምዕራፍ የሚለው በስሩ በርካታ ክፍሎችን እንዲይዝ መደረጉ ተገቢ ነው ብየ አላምንም፣ ይልቁንም መሆን የነበረበት የተገላቢጦሹ ነው፣ ምንያቱም በክፍል ስር በርካታ ምዕራፎች ሊኖሩ ይችሉ እንደሆነ እንጂ በምዕራፍ ስር ከንዑስ ምዕራፎች ያለፈ በርካታ ክፍሎች ሊኖሩ አይችሉምና ነው፡፡ ሌላው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር የሚለው በልዩ ሁኔታ መታየት ሲገባው በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ግን እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር የሚለው ነው በልዩነት የተቀመጠው፣ ምንም እንኳ አቶ ዓለምነው ይህን ማድረጋቸው በብዛት የውጭ መጽሀፍትን በዋቢነት ከመጠቀማቸው ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም መጽሀፉ ኢትዮጵያዊ በሆነው የአማርኛ ቋንቋ ጥርት ብሎ እስከተጻፈ ድረስ የዚህ አይነቱ አቀራረብ የተለመደ አይደለምና በወቅቱ መታረም ነበረበት፡፡

በሌላ በኩል በተለምዶ በአንድ መጽሀፍ ውስጥ ሊካተቱ ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ ምስጋናና መቅድም በቀዳሚነት ይገኙበታል፣ የምስጋና መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የሚሰጠው ገጽም ከሁሉም ቀድሞ መገኘት ሲገባው በመጽሀፉ መጨረሻ ላይ መወሸቁ ብዙም ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን ተገቢ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሰዎችንና ተቋማትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ በሚገባ አንዳይታወቅ ሊያደርግ ይችላልና እንደዛ ባይሆን ይመረጥ ነበር፡፡ ሌላው ከአቀራረብ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት የመቅድምና የመግቢያ አጻጻፍን የሚመለከተው ጉዳይ ነው፣ በዚህ መጽሀፍ ውስጥ መቅድም ተብሎ የቀረበው የመጽሀፉ መግቢያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ካልሆነ በስተቀር መቅድም ሊያሰኘው የሚያስችል ይዘተ አላገኘሁበትም፡፡

በእኔ እምነት መቅድም በዋነኛነት መጽሀፉን ለመጻፍ ያነሳሳውን ሁኔታ፣ በሒደቱ የተከሰቱ መልካምና ገፊ አጋጣሚዎች እንዲሁም የታለፉ ፈተናዎች በመጨረሻም የተደረሰበት ሁኔታና የወሰደውን ጊዜ በአጭሩ በማመልከት ተደራሲያን ለካ ይሄም ኖሯል እንዲሉ ለማድረግ የምንጠቀምበት ገጽ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታየት የነበረበት ሌላው ጉዳይ ደግሞ የግርጌ ማስታወሻና የዋቢ ጽሁፎች ዝርዝር በአንድ ላይ መቅረቡ ነው፡፡ በዚህ መጽሀፍ ላይ ሁለቱም በአንድ ላይ ተዘርዝረው የቀረቡበት ሁኔታ ታይቷል፣ የዚህ አይነት አቀራረብ ብዙም የተለመደ አይደለም ብቻ ሳይሆን ዋና ዋና የማጣቀሻ ጽሁፎችን በአግባቡ ለይተን እንዳንመለከት የሚያደርግ በመሆኑ ያን ታሳቢ ማድረግ ነበረበት፡፡

ይልቁንም የግርጌ ማስታወሻዎች በየገጹ ቢመለከቱና መጨረሻ ላይ ደግሞ የዋቢ መጽሀፍት ዝርዝር በፊደል ቅደም ተከተል ቢቀመጥ ኖሮ አንባቢ የተጠቀሰው ሀሳብ ከየትኛው መጽሀፍ ወይም ሰነድ ላይ እንደተወሰደ ለማረጋገጥም ሆነ ተጨማሪ ግንዛቤ ለማግኘት ቢፈልግ በቀላሉ ለማግኘት ያስችለው ስለነበር ይኸኛው አማራጭ ይበልጥ የተሻለ እንደነበር ከወዲሁ መገመት አይከብድም፡፡ ሌላው በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ያገኘሁት ለየት ያለ ነገር ደግሞ የኢታሊክስ አጠቃቀም ነው፤ በጥቅስ ውስጥ የሚቀመጡ ሀሳቦች በኢታሊክስ መልክ እንዲቀመጡ የሚደረገው በደራሲው አማካኝነት ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ የተተረጎሙ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ሁሉም በጥቅስ ውስጥ የሰፈሩ ሀሳቦች በኢታሊክስ መልክ እንዲቀመጡ ከመደረጉም በላይ ሁሉም በጥቅስ ውስጥ የገቡ ሀሳቦች ደምቀው እንዲታዩ ተደርጓል፣ ይህንንም አቀራረብ ደራሲው ተሳስቶ ቢጠቀምበት እንኳ በዋነኛነት የአርትኦት ስራውን በሀላፊነት ያከናወኑት ሰዎች ሊያስተካክሉት በተገባ ነበር፡፡

በመጽሀፉ ውስጥ የታየው የቋንቋ አጠቃቀም ሁኔታ
ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ አቶ ዓለምነው በሚገርም ሁኔታ የአማርኛ ቋንቋን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋላቸውን በልበ ሙሉነት መመስከር እችላለሁ፣ እሳቸውም በመቅድሙ ላይ አስቀድመው ለመግለጽ እንደሞከሩት አብዘሀኛው ሀሳብ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከተጻፉ መጽሀፍትና መጣጥፎች እየተሰደ የተተነተነ በመሆኑ በመጽሀፉ ውስጥ በርካታ የእንግሊዘኛ ቃላትን አገኛለሁ ብየ ጠብቄ ነበር፡፡ ሆኖም አቶ ዓለምነው የቻሉትን ያህል ጥረት በማድረጋቸው ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር የጎላ ስህተት ሳይፈጽሙ መቅረታቸውን ተመልክቻለሁ፣ እናም የዚህ አይነቱ ጥረት በእጅጉ ሊበረታታ ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡

ሆኖም ስራቸው አሁንም ከጉድለት የጸዳ አለመሆኑን አንዳንድ ምሳሌዎችን በማንሳት ለማሳየት ልሞክር፣ በቀላሉ ወደ አማርኛ ተመልሰው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ቃላት ወይም ሀረጋት በእንግሊዘኛ እንዳለ የተገለጹበት ሁኔታ ተሰተውሏልና ነው፡፡ ለምሳሌ ቶርቸር፣ ፌልድ ስቴትስ (ገጽ 9)፣ ኋይ ኔሽንስ ፌል (ገጽ 107)፣ ሲቪል ሰረቪስ በብዙ ገጾች ላይ፣ ካፒታል ከንዑስ ርዕሱ ጀምሮ፣ ማኑፋክቸሪንግ በተለዋጭነት እየገባ፣ ኦን ሶቭዮት ሶሻሊስት ወዘተ የሚሉት ባሉበት ሁኔታ ነገር ግን በአማርኛ ፊደላት ተጽፈው መግባታቸው በአንድ በኩል ቀጥተኛ የሆነ የአማርኛ ትርጉም ለመስጠት በማያስቸግሩበት ሁኔታ ለምን ጥቅም ላይ ዋሉ ያሰኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ያው የተለመደው የእንግሊኛ ቃላትን በየአጋጣሚው የመጠቀም ልማድ አቶ ዓለምነውንም ሙሉ ለሙሉ ያለቀቃቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከቋንቋ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ሌላው ጉዳይ የአማርኛ ቃላት ወይም ሀረጋት አጠቃቀማችን ላይ አልፎ አልፎ የሚስተዋል ግድፈት ወይም ጉድለት ነው፣ በዚህ ረገድ አቶ ዓለምነው በመጽሀፋቸው ላይ የተጠቀሙበትን አንድ ሀረግ ብቻ መዘን እንመልከት፣ ይኸውም “ድህነት አደር” የሚለው ሀረግ ነው፡፡

ይህ ሀረግ በተለምዶ አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ላብ አደር፣ ወዘተ. እንደሚባለው ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል፣ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ሀረጋት የአንድን የህብረተሰብ ክፍል የምጣኔ ሀብት መሰረት ወይም መተዳደሪያ አሊያም የስራ መስክ ለመግለጽ የሚያገለግሉ ሲሆን፣ ድህነት አደር የሚለው ሀረግ እስካሁን ድረስ በምንጠቀምበት የአማርኛ ቋንቋችን ውስጥ ትርጉም የለሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀን ተቀን ግንኙነታችን ተጠቅመንበት የማናውቅና በአማርኛ ተናጋሪው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሀረግም አይደለም፡፡

ስለሆነም እንደዚህ አይነት ለአብዛኛው ተደራሲ ብዙም ትርጉም የማይሰጡ ሀረጋትን ወይም ቃላትን ከመጠቀም ይልቅ የተለመዱና ስሜት ሊሰጡ የሚችሉ ሀረጋትን ብንጠቀም የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሌላ አነጋገር ለየት ያለ አቀራረብ የተጠቀምን መስሎን የምናስገባቸው ቃላት በአንድ በኩል ትርጉም የለሽ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል፣ በሌላ በኩል የተደራሲያንን ንባብ ያደናቅፋልና አስቀድሞ ማረሙ ሳይሻል አይቀርም፡፡

የመጽሀፉ ይዘት
ይህ መጽሀፍ በአብዛኛው ሁሉን አቀፍና በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰ በመሆኑ በአንድ መጽሀፍ ውስጥ የበርካታ ዘርፎችን ልምድ፣ ክህሎትና እውቀትን ለማግኘት እድል ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ፣ ሆኖም በርካታ ጽንሰ ሀሳቦችን በአንድ መጽሀፍ ውስጥ አጭቆ ለማቅረብ ከመሞከሩ ጋር ተያይዞ በአንድ በኩል የሀሳቦች መደጋገምን ሲጋብዝ በሌላ በኩል አንዳንድ መሰረታዊ ሀሳቦች በአጭሩ ተገልጸው እንዲያልፉ አድርጓቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ በዚ ረገድ ከደከሙ አይቀር ሰፋ ብለው ቢዳሰሱና በአዲስ መልክም ቢካተቱ ያልኋቸው የተወሰኑ ሀሳቦች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ ቀጥሎ በሚገኙት አንቀጾች በምሳሌ እያስደገፍሁ ለማሳየት ልሞክር፡፡

የአለም ባንክ፣ የአለም የገንዘብ ተቋምና የአለም የንግድ ድርጅት አሉታዊ ተጽዕኖ ጠቅለል ባለ መልኩ የተገለጸ ቢሆንም በአፍሪካ አገሮች ላይ በአጠቃላይና በኢትዮጵያ ላይ ደግሞ በተለይ የነበረው አሉታዊ ተጽዕኖ ምን ይመስል እንደነበር በምሳሌ ተደግፎ ቢገለጽ የተሟላ ስዕል ይሰጥ እንደ ነበር መገመት ይቻላል፡፡ ሌላው ቀደም ሲል የነበረው የኦሮሞ የገዳ ስርአት በተወሰነ መልኩ የተጠቀሰ ቢሆንም አሁን ባለው ፌዴራላዊ አደረጃጀት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግስት አተያይ ምን እንደሚመስል እንደመነሻ አለመውሰዱስ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ሀሳብ ላይ የተወሰነ ነገር ቢባል ነሮ ጥሩ ነበር፡፡

ከገጽ 107 አጋማሽ እስከ 112 አጋማሽ ድረስ ባሉት ገጾች ላይ ደግሞ ስለኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ሒደት የተቀመጠው ሀሳብ አጭር ከመሆኑ የተነሳ በተወሰኑ ገጾች ብቻ ቀንብቦ ማስቀመጥ ከሀገራችን ተሞክሮ ጋር በማያያዝ ብዙ ትምህርት እንዳይገኝበት ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ከዛም ባሻገር በአገር ውስጥ ምሁራን ስራዎች ላይ ተመስርቶ ትንሽ ቢዳብር መልካም ነበር፣ በዚህ ረገድ የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴንና የዶክትር አሰፋ ፍስሀ ስራዎችን በስፋት መጠቀም ይቻል ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የአቶ አለምነው መጽሀፍ ከመንግስት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ከኢህአዴግ ጽሁፎች ውጭ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ምሁራን ስራዎችን ወደ ጎን የተወ ይመስላል፣ ምናልባትም የዶክትር ምህረት ደበበን መጽሀፍ አንድ ጊዜ እንዲሁም አቶ አለሙ አበበ የተረጎሙትን መጽሀፍ ሁለት ጊዜ ጠቅሰው ካልሆነ በስተቀር የሀገራችን የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ሞያተኞች ስራዎች አለመዳሰሳቸው ለራሳችን የምንሰጠውን ትኩረት አናሳነት በግልጽ ያመለክታል፡፡

በዚህ አጋጣሚ አንድ ምሳሌ ልጨምርና የችግራችንን ስፋት ለማሳየት ልሞክር፣ የደቡብ ኮሪያ መሪዎች ችንግዶ የምትባል መንደር ነዋሪዎችን እንቅስቃሴ ከተመለከቱ በኋላ በተሞክሮነት ቀምረው ለሌሎች አካባቢዎች ማስተላለፋቸውን በምሳሌነት አንስተው ሰፊ ትንታኔ አቅርበዋል፣ የሚገርመው ነገር አቶ አለምነው ሩቅ ምስራቅ ኤዥያ ድረስ ርቀው ሳይጓዙ እሳቸው በሚያስተዳድሩት ክልል ውስጥ እሳቸው ከሚኖሩበት 77 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙት አውራምባዎች ከዚህች መንደር በተሻለ ደረጃ ሊቀመርላቸው የሚችል መልካም ተሞከሮ እንዳላቸው ጠጋ ብለው በመመልከት በጥሞና ቢመረምሩት ኖሮ ምንኛ ጠቃሚ ትምህርት ባገኙ ነበር፡፡        
ኪራይ ሰብሳቢ የሚለው ቃልና ሀረግ በመጽሀፉ ውስጥ እዚህም እዛም ተደጋግሞ ተጠቅሷል፣ ሆኖም ትርጉሙ ምን እንደሆነ፣ ታሪካዊ አመጣጡና አሁን ያለበት ደረጃ ግምት ውስጥ ገብቶ በሚገባ ቢተነተን እግረ መንገዱን በዚህ ቃል ወይም ሀረግ ላይ በበርካታ ሰዎች ዘንድ የተፈጠረውን ብዥታ መግፈፍ ይቻል ነበር፡፡ በእኔ እምነት ይኸ ሀረግ ለመባል የተፈለገውን ሀሳበ በትክክል የሚያስተላልፍ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ሌላው በምዕራፍ ሁለት ክፍል ሁለት በተለይም 2.3 ወይም ከገጽ 127-129 አጋማሽ ድረስ ያለው ሀሳብ ቀደም ብለው ባሉት ገጾች በሚገባ የተገለጸ ስለሆነ እንዲሁም ክፍል ስድስት ማለትም ከገጽ 373 እስከ 377 የተቀመጡት ሀሳቦች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የተደገሙ በመሆናቸው በዛ መልክ በድጋሜ መካተታቸው አስፈላጊ አልነበረም፡፡

ሌላው ከመጽሀፉ ገጽ 147-149 በተለይም በ5.3 እና በ5.4 ስር የሚገኙት ንዑሳን ርዕሶች ቢቀያየሩ ይበልጥ ስሜት ይሰጡ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፣ ምክንያቱም በመርህ ደረጃ የመንግስት ጣልቃ ገብነት የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ መታየት ስላለበት፡፡ አንዲሁም በ5.4 ላይ የተቀመጡት ሁለት ትልልቅ ሀሳቦች ከሁለት ተከፍለው በሚገባ መተንተን ነበረባቸው፣ ይኸውም በአንድ በኩል የሁለቱም ጽንሰ ሀሳቦች መነሻና መድረሻ የተለያየ ከመሆኑ አንጻር ራሳቸውን ችለው ቢዳሰሱ መልካም ይሆን ነበር፡፡ በሌላ በኩል ለህብረት ስራ ማህበራት ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ስለ አክሲዎን ማህበራት ምንም ያልተባለበት ሁኔታም ስለተፈጠረ ቀላል የማይባል ክፍተት እንዲኖር አድርጓል፡፡

ልብ ብሎ ለሚመለከት ሰው በሀገራችንም ሆነ በቀረው አለም የአክሲዎን ማህበራት ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፣ ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን እየታየ ያለውን የኢንቨስትመንት ሁኔታ ስንመለከት የአክሲዮን ማህበራት ድርሻ እጅግ ጉልህ ሆኖ እናገኘዋለን፣ በዚህ ረገድ በዋነኛነት የአክሲዮን ማህበራት በስፋት የተሳተፉባቸውን የባንክ፣ የኢንሹራንስና በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ኩባንያዎችን ወቅታዊ እንቅስቃሴ ብንመለከት የድርሻቸውን ጉልህነት መገንዘብ እንችላለን፡፡ ስለሆነም አክሲዮን ማህበራት ሚና በሚገባ ቢተነተን መልካም ነበር፡፡

ቅድመ 1983 ኢትዮጵያ ላይ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ዘርዘር ያለ ሀሳብ መቅረብ ነበረበት እላለሁ፣ ስለሌሎች አገሮች ቅድመ ታሪክ ሰፊ ሽፋን እየሰጡ መጥተው የራስን ማሳነስ ለራስ ሲቆርሱ የሚለውን አባባል የሚቃረን ሆኖ አግኝቸዋለሁ፣ በተለይም በንጉሱ የመጨረሻ የስልጣን ዘመን በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተጀምረው የነበሩት ዘመናዊ እርሻና የኢንዳስትሪዎች ማቆጥቀጥ፣ በደርግ ጊዜ በእጅጉ ተስፋፍቶ የነበረው የመንግስት እርሻና የህብረት ስራ ማህበራት እንቅስቃሴ በአዎንታም ሆነ በአለታ ብዙ ሊባልለትና ጠቃሚ የሆነ ትምህርትም ሊወሰድበት የሚገባ ጉደይ እንደነበር በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በዚህ ረገድ ጠቃሚ ልምድም ሆነ ትምህርት ከውጭ ብቻ ይገኝ ይመስል የራስን ወደ ጎን በመተው የውጭዎች ላይ መመስረት “የራስን ጥሎ የሰው አንጠልጥሎ” ሊያሰኝ ይችላልና በአግባቡ ቢታሰብበት መልካም ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሌላው በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ስለዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብም ሆነ አስፈላጊነት ላይ ብዙ ተብሏል፣ ሆኖም በኢህአዴግ የሚመራው የሀገራችን መንግስት ባለፉት 26 አመታት ከዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ አተገባበር ጋር ተያይዞ ያለበት ሁኔታ በምሳሌ ተደግፎ እንዲሁም እየገጠሙት የሚገኙት ተግዳሮቶች በምሳሌ ተደግፈው ቢገለጹ መልካም ትምህርት ይገኝበት ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ ጎልቶ መነሳቱ አይቀርም፣ በዚህ ረገድ በመጽሀፉ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቀርቧል፣ ሆኖም በአንድ በኩል በሀገራችን እስካሁን ድረስ ከተካሄዱት ምርጫዎች ምን ትምህርት አገኘን በሚለውና የተለያዩ የምርጫ ማስፈጸሚያ ስልቶችን መርጦ ስራ ላይ በማዋል ረገድ የታየው ክፍተት ከመብቶች ትግበራ ሒደት አኳያ የሚኖራቸውን አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተጽዕኖ መዳሰሱ ትርጉም የነበረው ይመስለኛል፡፡ ሆኖም መጽሀፉ ይህን ሁኔታ በለሆሳስ የዘለለው ይመስላል፣ በተረፈ በመጽሀፉ ውስጥ የተደጋገሙ ሀሳቦች ያሉ ቢመስልምና አንዳንድ ጠቃሚ ጉዳዮች ሳይዳሰሱ የቀሩ ቢሆንም ንድፈ ሀሳባዊ ትንታኔ ከተግባራዊ እንቀስቃሴ ጋር ተገናዝቦ የቀረበበት ስለሆነ ጠቃሚ ትምህርት እንደሚገኝበት ይታመናል፡፡ 

No comments:

“ምስ ህዝቢ ምርኻብ ፍርቂ መንገዲ ዓወት‘ዩ”

Tigrai Online “... ገፅ መራሕትና ካብ ዘይንርኢ፣ ንመራሕትና ካብ እንናፍቖም ዳርጋ 20 ዓመታት ኣቚፂርና፡፡  ናብ ከባቢና ሓንቲ መኪና እንተመፂኣ ኣንታ መን‘ኮን ሒዛ መፂኣ ? እናበልና ብሃንቀውታ ነመዓዱ፡፡...